2020-የኢትዮ ጀርመን ዝግጅት በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ተሰረዘ

የተከበራችሁ የኢትዮ ጀርመን የስፖርትና ባህል ማህበር ቤተሰቦች, 
በአሁኑ ወቅት በአለም ዙሪያ በቅጡ ሊያዝና ሊጨበጥ ባልተቻለ ሁኔታ፡ በአደገኛ የመሰራጨትና የመዛመት ባህሪው ዘር ቀለም ሃብትና ቦታን ሳይመርጥ ሁሉንም የሰው ዘር በእኩል ደረጃ በማጥቃት ላይ የሚገኘውን የኮሮና ቫይረስን አስመልክቶ በተለያዩ ሚዲያዎች በየእለቱ  የተለያዩ እውነታውች እየቀረቡ ይገኛሉ።  

የዚህን ቫይረስ  ስርጭት ለመገደብና የህብረተሰቡን ጤና ለማስጠበቅ ሌት ተቀን ደፋ ቀና የሚሉት  የዓለማችን የህክምና ጠበብቶች ችግሩን ብቻቸውን  ለማስቆም እንደማይችሉና ከመቼውም ጊዜ በበለጠ የሁሉንም ህብረተሰብ እገዛ የሚሹበት ወቅት መሆኑን በተደጋጋሚ እየገለጹ ይገኛሉ።  

የኢትዮ ጀርመን የስፖርትና ባህል ማህበር ዓመራር ኮሚቴም ጉዳዩን በቅርብ ሲከታተል ቆይቶ በ22.03.2020 ባደረገው አስቸኩዋይ ስብሰባ  የማህበሩን ቀጣይ እንቅስቃሴዎች አስመልክቶ  ውሳኔዎችን አስተላልፎዋል።

በዚህም መሰረት በየዓመቱ የፊንግስተን የእረፍት ቀናት  ላይ  (Pfingsten Ferien) የሚዘጋጀው የኢትዮ-ጀርመን የስፖርትና ባህል ዝግጅት በዚህ ዓመት በ2020 በሃንቡርግ ከተማ ከኢትዮ ሃምቡርግ ማህበር ጋር በመተባበር  ሊያዘጋጅ የነበረውን  ዓመታዊውን ዝግጅት በተመሳሳይ ቀን በ2021 ለማዘዋወር በሙሉ ድምጽ ወስኖዋል።

የ2020 አዘጋጅ  የነበረው የኢትዮ ሃምቡርግ ማህበርም የተፈጠረውን ወቅታዊ ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት የፈጣሪ እገዛ ታክሎበት ቀጣዩን  ዝግጅት በማዘጋጀት ወገኖቻችንን  ዳግም ከሙሉ ጤና ጋር አንድ መድረክ ላይ እንደሚያገናኙልን ፈጣሪ ይርዳቸው።  

የተከበራችሁ የኢትዮ ጀርመን የስፖርትና ባህል ቤተሰቦች, ወቅቱ ሁላችንም በግልም ሆነ በጋራ ትልቅ ሃላፊነት በመውሰድ  በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕይወቶችን ለማዳን ምክንያት መሆን የምንችልበት ወቅት ነው። በመሆኑም የኮሮና ቫይረስን  ስርጭትን ለመግታት  ከተለያዩ የጤና ባለሞያዎችና  የህክምና ጠበብቶች የቀረበውንና ሁላችንም  ልናደርጋው የምንችለውን የመከላከያ መንገዶች  ህብረተሰቡ በቸልተኝነት  ሳይመለከታቸው  በተግባር  ያውላቸው ዘንድ መምከር ይገባናል።

የግል ንፅህናን መጠበቅ እና ለተወሰነ ግዜም ቢሆን አላስፈላጊ ማህበራዊ ግንኙነቶችን  በመቀነስ ችግሩን ለመፍታት በጋራ መስራት እንዳለብን በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ  ማሳወቅና እኛም በተግባር ላይ ማዋል ይጠበቅብናል።  
ጤና ይቀድማልና „Healthy First“ ሁላችንም በጋራ እንስራ። ሁላችንም ሃላፊነታችንን እንወጣ።

ፈጣሪ ምህረቱን ያውርድልን
የኢትዮ ጀርመን የስፖርትና ባህል ማህበር

Follow by Email
YouTube
Instagram